
ቅዳሜ ጥር 24/2017 ዓ.ም. ምሽት በጥይት ተደብድበው የተገደሉት የጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ክፍል ኃላፊ ዶ/ር አንዱዓለም ዳኜ ግድያቸው የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎችን እና የህክምናውን ማኅበረሰብ አስደንግጧል።
"በስንት ዘመን አንዴ የሚፈጠር ልጅ ነው" ሲሉ ዶ/ር አንዱዓለምን የሚገልፆቸው አብሮ አደጋቸው እና የሙያ አጋራቸው፤ ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ ሦስት ዩኒቨርስቲዎችን ባዳረሰው የሕክምና ትምህርታቸው ተሸላሚ እንደነበሩ ያነሳሉ።
"በዘመን እና በጊዜ መሀል ብቅ ከሚሉ ዓለም አቀፍ ጭንቅላቶች አንዱ ነው" ሲሉ የሚገልፆቸው ሌላ የቅርብ ጓደኛቸው፤ ምድር ላይ ከኖሩበት 37 ዓመታት 26ቱን ትምህርት ላይ ማሳለፋቸውን ገልፀዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የዶ/ር አንዱዓለም ወዳጆች እና ባልደረቦች ከግላዊ ሰብዕናቸው ጀምሮ አንቱታን ያተረፉ ሐኪም እንደሆኑ ይመሰክራሉ።
"ሕክምና ማንን ይመስላል ከተባለ ዶ/ር አንዱዓለምን ነው የሚመስለው" ሲሉም የሙያቸው ቁንጮ እንደሆኑ የሚያሰምሩ አንድ አብሮ አደጋቸው እና የሙያ አጋራቸው፤ በሁሉም ዘርፍ የተካኑ ነበር ይላሉ።
"ክፉ የማይወጣው፤ ታካሚዎቹን በሙሉ በእንክብካቤ የሚያክም" ሲሉ ሰብዓዊነታቸውን የሚገልፁት ወዳጃቸው "ታካሚዎችን በመንከባከብ፤ በማከም ብቻ ሳይሆን አንድ ሐኪም ከዕውቀት ባለፈ ታካሚዎችን የሚይዝበት መንገድ ምን ይመስላል ከተባለ ዶ/ር አንዱዓለምን ነው የሚመስለው" ብለዋል።
ዶ/ር እንዱዓለም ዳኜ በኢትዮጵያ የላቀ የካንሰር ቀዶ ሕክምና ማዕከል ማቋቋም ህልማቸው እንደነበር የጥበበ ጊዮን ሆስፒታል ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር የሺጌታ ገላው ተናግረዋል።
በካንሰር ለሚሰቃዩ ሕሙማን "ጥራት ያለው ሕክምና ከሰብዓዊ ግልጋሎት ጋር" መስጠት የሚችል ማዕከል በማቋቋም ከሕክምና ባለፈ ለታካሚዎች እና ለቤተሰቦቻቸው ተስፋ፣ ድጋፍ እና ሰብዓዊ ክብር እንዲያገኙ ሩቅ አልመው በቅርብ መቅረታቸውን ጠቁመዋል።
"ካለው ሰብዕና፣ ከሚሰጠው አገልግሎት እና ካለው ተቀባይነት አንፃር" ግድያው እንደረበሻቸው ያልደበቁ ሌላ ባልደረባቸው፤ ግድያውን "የሙያን ድንበር የጣሰ" ብለውታል።
"ከባህሪ እስከ እውቀት" ተክነዋል የተባሉት ሐኪም ቅዳሜ ጥር 24/2017 ዓ.ም. ከባሕር ዳር ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ ቆሼ በተባለ አካባቢ ደረታቸውን በጥይት ተመተው ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን፤ ግድያው ከፍተኛ ድንጋጤን ፈጥሯል።
"[ሞትን] እሱ ላይ የምጠብቀው አልነበረም። ምናልባት ብዙዎቻችን ካለቅን በኋላ፤ መጨረሻ ላይ ለሞት ይታጫል ብለን የምናስበው ሰው በእንደዚህ ዓይነት አደጋ መሞቱ. . ." አስደንጋጭ መሆኑን ተናግረዋል።
ዶ/ር አንዱዓለም በባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ስር የሚገኘው ጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የጉበት፣ የቆሽት ሰብ እና የሃሞት ከረጢት ስፔሻሊት ሐኪም፣ ተመራማሪ እንዲሁም መምህር ነበሩ።
በዩኒቨርስቲው ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር አንዷለም ዳኜ የጉበት፣ የሀሞት ከረጢት እና የቆሽት ሰብ ስፔሻላይዜሽን ትምሕርታቸውን ባለፈው ዓመት ነበር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያጠናቀቁት።
በባሕር ዳር ከተማ በትርፍ ሰዓት ከሚሠሩበት አፊላስ ሆስፒታል ሥራቸውን ጨርሰው ከከተማ 10 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ወደሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው (የሆስፒታሉ ባለሞያዎች መኖሪያ) እየተመለሱ ሳለ ነበር አመሻሽ 12፡30 አካባቢ የተገደሉት። (BBC Amharic)
#Dr Andualem Dagne @HagereMedia #Hageremedia